ሪፖርት | የሊጉ መሪ ከናፈቀው ድል ጋር ታርቋል

ሪፖርት | የሊጉ መሪ ከናፈቀው ድል ጋር ታርቋል

ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማን 3ለ0 በማሸነፍ ከአራት ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ዳግም ወደ ድል ተመልሷል።

ቀዝቀዝ ካለ አጀማመር በኋላ ደቂቃዎች ሲሄዱ ወደፈጣን ሽግግር ያመራው ጨዋታው 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች የመጀመሪያ ግብ አግኝተዋል። ሬድዋን ናስር ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ደስታ ደሙ ጨርፎ ሲያሻግራት መስፍን ታፈሰ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከግቡ በኋላም ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚዎቻቸው መድረስ የቻሉ ቢሆንም ይሄ ነው ተብሎ የሚገለፅ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ አላደረጉም።

የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረቸው ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል፤ ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ ከራሳቸው ግብ ክልል በረጅሙ የጣለውን ኳስ ብርሃኑ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ብቻውን ለነበረው መስፍን ታፈሰ አሻግሮለት በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ አጋማሹ 2ለ0 ተጠናቋል።

አዞዎቹ ተጠናክረው በተመለሱበት በሁለተኛው አጋማሽ ወደፊት እየገቡ የሲዳማ ቡናዎችን ተከላካይ መፈተን ችለው የነበረ ቢሆንም አደገኛ ሙከራም ሆነ አስቆጪ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ሲዳማ ቡናዎች በአንፃራዊነት በመልሶ ማጥቃት እየገቡ መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረለትን ኳስ ፈድሪክ ኑሲ ከግብ ጠባቂው ፈትለፊት ተገናኝቶ የመታው ኳስ ጠንካራ ሳይሆን የቀረው ሌላ ግብ ሊያስገኝላቸው የቀረበ አጋጣሚ ሲጠቀስ በመስመር በኩል እየገባ ተከላካዮችን ሲፈትን የነበረው መስፍን ታፈሰ 78ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ኤፍሬም ታምራት ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ በራሱ ግብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው 3ለ0 እንዲሆን አድርጎ ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ሲዳማ ቡናዎችን ከናፈቃቸው ድል ጋር በማስታረቅ ጨዋታው ተጠናቋል።