ምክትል ከንቲባው የተገኙበት ውይይት ተደረገ

በአዲስ አበባ የሚገኙ የፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ክለቦች አመራሮች እንዲሁም ደጋፊዎች የታደሙበት የምክክር ጉባዔ ቀትር ላይ በኢንተርኮንትኔታል አዲስ ሆቴል ተካሄደ።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአዲስ አበባ መስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኩማ (ኢንጂነር) ፣ የመስተዳድሩ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እና የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሐ (ኢንጂነር) ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ፣ የክለብ አመራሮች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ቁጥራቸው በርከት ያሉ ደጋፊዎችም ታድመው ነበር።



በውይይቱ ላይ ለከተማዋ ከንቲባ እና ለሚመለከታቸው አካላት በርከት ያሉ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በዋናነት ከተነሱት መካከል;- 

* የከተማዋ የስፖርት ማዘውተርያ ሥፍራ ችግሮች ከፍተኛ ትኩረት ይደረግባቸው ፤  ለነገው ትውልድ ይታሰብ የወጣቶች አስፋልት ላይ መጫወት ይቁም…

* ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቤት እና የቀበሌ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር ፤ አሁን ቀርተዋል እንዲቀጥሉ ይደረግ…

*  ደጋፊዎች በክልል ጨዋታ ለመመልከት በምንሄድበት ወቅት የሚደርስብን ግፍ እና በደል እንዲቆም  የአዲስ አበባ መስተዳደር ክትትል ያድርግልን…

* ፀጥታ አስከባሪዎች እና የሚዲያ አካላት ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተጨማሪ መንስኤ በመሆናቸው ማስተካኪያ ሊደረግ ይገባል…

* የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። የውጪ ተጫዋቾች ይምጡ ሆኖም ቁጥራቸው ይገደብ  ፤ ለታዳጊዎችም ዕድል ይሰጥልን….

* ወደፊት እንደነዚህ ያሉ የውይይት መድረኮች በሦስት ወር አንዴ ቢዘጋጁልን…

* እንደ ሀገር ማሰብ እየቀረ የእግርኳሱ የዘረኝነት እና የፖለቲካ መናህርያ ሆኗል ፤ ይህ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል…

የመጨረሻው ጠያቂ የቅዱስ ጊዮርጊስ አስጨፋሪ ይድነቃቸው (አቸኖ) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ የሆነው አንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተን ማሰብ ይገባናል በማለቱ የህሊና ፀሎት በማድረግ የቀጠለው ጉባዔ በተከታይነት ወደ ምላሽ አምርቷል።

ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት  አቶ ኢሳይያስ ጅራ በተሰጠው ምላሽ እግርኳሱ ጎጠኝነት ፣ ዘረኝነት ገብቶበታል ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል ፤ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ውድድሮች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑ ሁላችንም በጋራ መስራት አለብን ፣ የፍትህ አካላት ፣ የስታድየም ገቢን በተመለከተ የነበሩብንን ችግሮች አስተካክለን እንሄዳለን ፤ ቃልም እንገባለን። የስፖርት ማዘውተርያ ጉዳይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ያሳስበዋል ትኩረት ይሰጠው። በእኛ በኩል ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀስን በመሆኑ ሁላችሁም ከጎናችን እንድትሆኑ የሚሉት ሀሳቦች ተነስተዋል።



የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ በበኩላቸው የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነና በቀጣይ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ከሁሉም ክለብ ደጋፊዎች ተቀራርበን አብረን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኩማ (ኢንጂነር) ይህ መድረክ የመጨረሻችን አይደለም በቀጣይ ተመሳሳይ መድረኮች ስለሚኖሩ እንወያያለን። በስፖርት ማዘውተርያ ዙርያ አሁን ብዙ አላወራም፤ ችግሩን በሚገባ አውቃለው፤ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራበታለን። የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ከሁሉም የክልል ከተሞች ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር አንድ ላይ እንሰራለን። የሀገራችን እግርኳስ እንዲያድግ መስተዳድሩ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ እናደርጋለን። ብዙ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን እንሰራለን በሚሉት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ማብራሪያ ሰጥተዋል።