ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ ፊታቸውን ወደ ደቡብ አሜሪካ አዙረዋል

ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጭ አሰልጣኞች ቅጥር ፊታቸውን ያዞሩት ፈረሰኞቹ ይበልጥ ወደ ደቡብ አሜሪካ ትኩረታቸውን ማድረጋቸው ታውቋል ።

ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት መጀመርያ በውጤት ማጣት ምክንያት አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶን በማሰናበት አሰልጣኝ ስቴዋርት ሀልን ቀጥሮ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን እንግሊዛዊው አሰልጣኝ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በራሳቸው ፍቃድ ከክለቡ ጋር በመለያየታቸው ምክንያት ቡድኑ ቀሪ የሊግ 6 ጨዋታ (3 ጨዋታዎች በፎርፌ አልተካሄዱም) በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ አድርጓል። ይህን ተከትሎም ለቀጣዩ ዓመት ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ለመቅጠር እያደረገ የነበረውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በመተው ስማቸው ለጊዜው ባይጠቀስም ፊቱን ወደ ላቲን አሜሪካ አሰልጣኞች አዙሯል። ክለቡ በቅርቡ ቅድመ ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ ከመጀመሩ በፊትም የአሰልጣኝ ቅጥሩን እንደሚያጠናቅቅ ተነግሯል ።

ከደቡብ አሜሪካ አሰልጣኞች ጋር በተያያዘ ፈረሰኞች ከዚህ ቀደም የብራዚላዊው ኔይደር ዶ ሳንቶስን በ2007 ቀጥረው ያልተሳካ ግማሽ ዓመት ቆይታ እንደነበራቸው የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡