ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ነጥብ ተጋርተዋል

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በአምስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጀመርያ 11 ቴዎድሮስ በቀለን በአማኑኤል ጎበና በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል። ተጋባዦቹ ጅማ አባጅፋሮች በበኩላቸው የዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ካስመዘገቡበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ኤርሚያስ ኃይሉ እና ጀሚል ያዕቆብን በአምረላ ደልታታ እና ሱራፌል ዐወል ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ የጅማዎችን የግብ ክልል መጎብኘት የጀመሩት አዳማዎች ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችን በማድረግ ጫናዎችን መፍጠር ጀምረዋል። ጨዋታው በተጀመረ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥም ከነዓን ማርክነህ እና ዳዋ ሆጤሳ ከመስመር ያገኙትን ኳስ ወደ ግብ መተው መክኖባቸዋል። በተቃራኒው እጅግ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ጨዋታውን የጀመሩት ተጋባዦቹ ለአዳማዎች ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ ለቀውላቸው ተንቀሳቅሰዋል።

አዳማዎች ተጋጣሚያቸው የፈቀዱላቸውን የመጫወቻ ሜዳ በመጠቀም ከየአቅጣጫው ጥቃቶችን መሰንዘር ቀጥለዋል። በዚህም በ9ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ዳዋ በደረቱ ለከነዓን አመቻችቶለት ከነዓን በሞከረው እንዲሁም ከደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ በረከት ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከነዓን በግምባሩ ለማስቆጠር በጣረው አጋጣሚ እጅግ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።
ጅማዎች ከ12 ደቂቃ በኋላ በተገኙ ተከታታይ የቅጣት እና የመዓዘን ምቶች ወደ አዳማ የግብ ክልል በመድረስ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በተቃራኒው ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች በተለይ ከመስመር ላይ ግቦችን መፈለግ ቀጥለዋል። በዚህም ግዙፉ ተከላካይ ምኞት ደበበ ከመስመር ጥሩ ኳስ ተሻግሮለት ሳይጠቀምበት የቀረው እና ብሩክ ቃልቦሬ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ የመታው አጋጣሚዎች በቡድኑ በኩል አስቆጪ አጋጣሚዎች ነበሩ። ከመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች ብቻ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ያለሙ የሚመስሉት ተጋባዦቹ በ26ኛው ደቂቃ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አዳማ ግብ ክልል ቀርበው ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ ኤሊያስ አህመድ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ሄኖክ ገምቴሳ ወደ ግብ መቶት ግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ አድኖበታል።

የጨዋታ ብልጫቸውን በግብ ማጀብ ያልቻሉት አዳማዎች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ኳስን በትዕግስት መቀባበል መርጠው ተንሳቅሰዋል። ይህ የአዳማዎች የጨዋታ ምርጫ የጠቀማቸው የሚመስሉት ጅማዎች ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ ወደፊት ወተው ለመጫወት ጥረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ፈጥኖ በመሮጥ ያገኘው ዳዋ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሃብታሙን አልፎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ተጨዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ይህንን አጋማሽ በፍጥነት ያልጀመሩት ባለሜዳዎቹ ኳስን መቆጣጠር አላማ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃራዊነት ተሻሽለው የቀረቡት ጅማዎች በበኩላቸው እንደ አዳማ አጨዋወት እራሳቸውን እየገደቡ ውጤት ይዞ ለመውጣት ጥረዋል። በ51ኛው ደቂቃም ንጋቱ ሃ/ስላሴ ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከደቂቃ በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት አዳማዎች በረከት ከተከላካይ ጀርባ የተላከለትን ረጅም ኳስ ተጠቅሞ በሞከረው ሙከራ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።

ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ዳግም ወደ ጅማዎች የግብ ክልል የደረሱት አዳማዎች በከነዓን አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል። የባለሜዳዎቹ የፊት መስመር ተጨዋች ዳዋ በ64 እና በ68ኛው ደቂቃ ከርቀት በተመታ እና ከመዓዘን በተገኘ የግምባር ኳስ ተጨማሪ ሙከራ አድርጓል። በመጀመሪያ እቅድነት ወደ ሜዳ ይዘውት የገቡት እቅድ ፍሬ አላፈራ ያላቸው አዳማዎች ከ68ኛው ደቂቃ በኋላ በ3 ተከላካይ ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም ፈጣን የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የመስመር ተጨዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ አስገብተው በተሻለ ግቦችን ለማግባት ጥረዋል።

በሚፈልጉት መልኩ ጨዋታው እየሄደላቸው ያለው ጅማዎች በ72ኛው ደቂቃ በአምበላቸው አማካኝነት ከርቀት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው የመጨረሻ እድላቸውን ለመጠቀም ወደ ጅማዎች ክልል ያመሩት አዳማዎች ተቀይሮ በገባው ሃይሌ እሸቱ እና በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ዳዋ ሆጤሳ አማካኝነት ሙከራ አድርገው ወጥቶባቸዋል።

ጨዋታውም 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አራተኛ ተከታታይ ጨዋታውን አቻ የተለያየው አዳማ ስድስተኛ ደረጃ ሲቀመጥ ጅማ አባ ጅፋር 11ኛ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ