በትግራይ እግርኳስ ትልቅ ድርሻ ያላቸው የእምነት አባት

ላለፉት ሀያ ዘጠኝ ዓመታት በታዳጊዎች እግርኳስ ስልጠና የሰሩት አቦይ ቀሺ ገብረመስቀል አብርሀ

በተለምዶ የእምነት አባቶች በእግርኳስ ላይ ድርሻ ሲኖራቸው የተለመደ ባይሆንም በመቐለ ነዋሪነታቸውን ያደረጉትና ላለፉት ሀያ ዘጠኝ ዓመታት በእግር ኳስ አሰልጣኝነት እየሰሩ የሚኙኘት አንድ የእምነት አባት ይገኛሉ። በአከባቢው የእግርኳስ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው እና በታዳጊዎች እግርኳስ በርካታ ሥራዎች በመስራት በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለተጫወቱት ሚካኤል ደስታ፣ አማኑኤል ግደይ፣ አርዓዶም ገብረህይወት እና ሌሎች በታዳጊ ፕሮጀክት ደረጃ ያሰለጠኑት አቦይ ቀሺ ገብረመስቀል አብርሀ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ሰባ ዓመታቸው ላይ ሆነውም ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት እኚህ የእምነት አባት በ1983 ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በታዳጊዎች እግርኳስ መሳተፍ የጀመሩ ሲሆን ከሦስት ዓመት የመቐለ ቆይታ በኋላ ነበር በ1986 በከተማው የስፖርት አስተባባሪ በመሆን ሥራ የጀመሩት። ከእምነት አባትነታቸው ጎን ለጎን በእግርኳሱ መስራታቸው አዲስ ነገር በመሆኑ በአንድ ወቅት በክልሉ የእግርኳስ እንቅስቃሴ አተኩራ በሁለት እትሞች ከታተመችው ባሎኒ ከተባለች መፅሐፍ ጋር ባደረጉት ቆይታ በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ መስቀል ይዘው በመታየታቸው ብዙ ወቀሳዎች ይደርሳቸው እንደነበር ገልፀው ነበር።

04 (እንዳ ፀባ) በተባለ ሰፈር የእስልምና ተከታይ የሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ባዘጋጁት እና ቢላል 1፣ ቢላል 2፣ ቢላል 3 እና ቢላል 4 የተባሉ ቡድኖች የተሳተፉበት ውድድር ተጋብዘው ውድድሩን ካዩ በኋላ በታዳጊዎች ዙርያ ለመስራት ፍላጎቱ እንዳደረባቸው ከመፅሐፉ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት አቦይ ቀሺ በወቅቱ ለአስራ ሦስት ዓመታት የዘለቀ ዓመቱን ሙሉ የሚካሄድ ውድድር እንደነበራቸውም ገልፀው ነበር።

በአሰልጣኝነት የ’ B ‘ ላይሰንስ ያላቸው አቦይ ቀሺ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የተጫወቱ 21 ተጫዋቾች በከፍተኛ ሊግ ደረጃ የተጫወቱ ደግሞ 48 ተጫዋቾች በድምር በድምሩ 69 ተጫዋቾች ለሀገሪቱ እግርኳስ እንዳበረከቱ ከመፅሀፉ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቦይ ቀሺ በተለይም ወደ እግርኳስ በገቡባቸው መጀመርያ ዓመታት በርካታ ተቃውሞዎች እንደነበሩ ገልፀዋል። ” ቄስ ሆኖ እንዴት ወደ እግር ኳስ ይገባል በሚል ከአከባቢ ማሕበረሰብ እና ከቤተሰብ ሳይቀር ተቃውሞዎች ነበሩ፤ አሁን ግን በጣም ቀንሷል። በአንፃሩ እንደውም ድጋፎች አሉ። እግር ኳስ ማሰልጠን ከመፅሀፍ ቅዱስ ህግ ጋር የሚፃረር ነገር ስለሌለው ማሰልጠኔን ቀጥያለው። ” ብለዋል።

በአስተባባሪነት ከእግርኳስ ጋር ተዋውቀው በ1988 የአሰልጣኝነት ስልጠና ወስደው ላለፉት ዓመታት በታዳጊዎች ስልጠና ላይ እየሰሩ የሚገኙት ቄስ ገብረመስቀል አብርሀ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ከቀናት በኋላ የምናቀርብላችሁ ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ