ዜና እረፍት | ፌዴራል ረዳት ዳኛ ብርሀኑ ይቱ በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ አለፈ

በ2013 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከሚያድጉ ዳኞች መሐል አንዱ የነበረው ፌዴራል ረዳት ዳኛ ብርሀኑ ይቱ ዛሬ ማለዳ በልምምድ ላይ እያለ የመኪና አደጋ አጋጥሞት ህይወቱ አልፏል፡፡

ፌዴራል ረዳት ዳኛ ብርሀኑ ይቱ ከአዲስ አበባ የዲቪዚዮን ውድድር የጀመረው የዳኝነት ህይወቱ ዛሬ ላይ በከፍተኛ ሊጉ በድንቅ ብቃታቸው ከሚያጫውቱት መካከልም ስሙ ይጠቀሳል፡፡ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በረዳት ዳኝነት ዘንድሮ ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ እያገለገለ የቆየ ሲሆን ዛሬ ማለዳ ግን 2013 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከሚያሳድጋቸው ዳኞች መካከል ስሙ ቢሰፍርም በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል፡፡ ዛሬ ጠዋት ከመኖሪያ ሰፈሩ ቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከእህቱ ባለቤት ጋር ልምምድ በመስራት ላይ ሳለ አንድ መኪና ትለማመድ የነበረች ሴት አቅጣጫ ስታ ከመንገዱ በመውጣቷ በልምምድ ላይ የነበረውን ብርሀኑን ህይወት ቀጥፋለች። ዳኛው ወደ ሆስፒታል ቢያመራም ህይወቱን ማዳን ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ፌዴራል ረዳት ዳኛ ብርሀኑ ይቱ ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅም አባት ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ በፌዴራል ዳኛ ብርሀኑ ይቱ ሞት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቡ ለጓደኞቹ እና ለወዳጆቹ መፅናናትን ትመኛለች፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!