ዋልያዎቹ ኒያሜ ደርሰዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ኒጀር ደርሷል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኮትዲቯር፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎቸን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎችን ለማድረግ የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ቡድኑም በትናንትናው ዕለት የመጨረሻ ልምምዱን መቀመጫውን አድርጎበት በነበረው የካፍ የልህቀት ማዕከል ካከናወነ በኋላ ዛሬ ረፋድ 5 ሰዓት ወደ ኒጀር ኒያሜ ተጉዟል።

23 ተጫዋቾችን ጨምሮ 35 አባላትን በመያዝ 5 ሰዓት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ልዑካኑ 10:15 በሰላም ኒያሜ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ቡድኑ የኒጀር ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ኒያሜ ከደረሰ በኋላም ማረፊያውን ኑም ሆቴል ኒያሜ ማድረጉ ታውቋል።

ቡድኑ የፊታችን ዓርብ ምሽት 1 ሰዓት የምድቡ ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን አከናውኖ ቅዳሜ ወደ ሀገሩ እንደሚመለስ ተሰምቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!