ሪፖርት | ዳዋ ሆቴሳ በደመቀበት ጨዋታ ሀዲያ ሊጉን በድል ጀምሯል

በዛሬው የሊጉ ውሎ መጀመሪያ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን 2-1 አሸንፏል።

ተመጣጣኝ ፉክክር የተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ለማስተናገድ ብዙ ደቂቃ አልወሰደበትም። ከግራ መስመር ይነሳ የነበረው ቸርነት ጉግሳ ከራሳቸው የግብ ክልል በበረከት ወልዴ የተሻገረለትን ኳስ ይዞ ከተከላካዮች በማምለጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ቀለል ባለ አጨራረስ ከመረብ በማገናኘት ድቻ በ4ኛው ደቂቃ እንዲመራ አስችሎታል። ከጅምሩ የተሻለ መነቃቃት ታይቶባቸው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በእድሪስ ሰዒድ አማካይነት ኢላማውን የጠበቀ ሌላ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በሒደት የማጥቃት ጫናቸው እየቀዘቀዘ ቢሄድም ካገኟቸው የማዕዘን ኳሶች ሙከራዎችን ለማድረግ ሲጥሩም ታይተዋል። ሆኖም አማካይ ክፍል ላይ የተጋጣሚያቸውን የኳስ ፍሰት ለመግታት ከሚያረጉት ጥረት መጠነኛ ስኬት ውጪ ጨዋታውን በጀመሩበት መንገድ የሀዲያን የኋላ ክፍል በቅብብሎች ደጋግሞ ማለፍ አልሆነላቸውም።

በቶሎ ግብ ያስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ተረጋግተው ወደ ቅርፃቸው ለመመለስ እና ኳሱን የተሻለ ለመቆጣጠር ብዙ ጊዜ ባይወስድባቸውም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ግን ቀላል አልሆነላቸውም። መሀል ላይ የተጋጣሚያቸውን የቁጥር ብልጫ በመቋቋም በግራ በመድሀኔ ብርሀኔ ፍጥነት፣ በመሀል በዳዋ ሆቴሳ ተለዋዋጭ የአጥቂ ጀርባ እንቅስቃሴ፣ በቀኝ በሱለይማን ሀሚድ ተሻጋሪ ኳሶች ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ከዳዋ ሆቴሳ እና ከመድሀኔ የርቀት ሙከራዎች በኋላ የቡድኑ ከባድ ሙከራ የተደረገው 39ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የሱለይማን ሀሚድ የቀኝ መስመር ክሮስ ሳጥን ውስጥ በአዲስ ህንፃ በጥሩ ሁኔታ ሲመቻች ሳሊፉ ፎፋና ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ በኃይል የመታው ኳስ ለማመን በሚከብድ መልኩ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከእረፍት መልስ ድቻዎች ከማጥቃቱ ቆጠብ ብለው በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን የመረጡ ሲመስሉ ሀዲያዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረታቸውን የቀጠሉ ሲሆን የአጋማሹ ጅማሮ ቀዝቀዝ ብሎ ታይቷል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ግን ከግራ መስመር እየተነሳ በሳጥኑ አካባቢ በግሉ ክፍተት ለመፍጠር ሲጥር የነበረው ዳዋ ሆቴሳ ላይ ጥፋት ተሰርቶ ዳዋ ራሱ በቀጥታ በመምታት ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አስቆጥሯል። ከአቻነቱ ግብ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ወደ ተሻለ መነቃቃት የተመለሰባቸው እንቅስቃሴዎች ማስተናገድ ችሏል። የማጥቃት ድክመታቸውን ለማረም ኤልያስ አህመድ እና በረከት ወንድሙን ቀይረው ያስገቡት ድቻዎች መጠነኛ መሻሻል ሲያሳዩ ሀዲያዎችም ቀጥተኛነት እየተንፀባረቀበት በመጣው አጨዋወታቸው ሌላ ግብ ፍለጋ ለማጥቃት ሞክረዋል።

በተለይም የኤልያስ አህመድ መግባት በፈጣን ሽግግር በቀኝ መስመር አድልተው ክፍተት እንዲፈጥሩ በር የከፈተላቸው ድቻዎች አልፎ አልፎ እስከሳጥኑ ውስጥ መዝለቅ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥሩም ለፊት አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ ያለቀ የግብ ዕድል መፍጠር ተስኗቸዋል። ይልቁኑም የዳዋ ሆቴሳን ፍጥነት ለመጠቀም ኳሶችን ወደ እሱ ማሳለፍ ያዘወተሩት ሀዲያዎች ተሳክቶላቸዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ከኋላ የተላከለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በተከላካዮች መሀል ሰንጥቆ ሳሊፉ ፎፋናን ቀይሮ የገባው ዱላ ሙላቱን ከግብ ጠባቂው ጋር ሲያገናኘው ዱላ በድንቅ አጨራረስ አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይሮታል። ሀዲያዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ጥንቃቄ ጨምረው በመጨረስም የ 2-1 ድልን ማጣጣም ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ