የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-2 ወላይታ ድቻ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች አሰተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው…

ነጥብ ማግኘታችን ትልቅ ነገር ሆኖ ጨዋታው ሁለት ዓይነት መልክ አለው ማለት እችላለሁ። የመጀመሪያው 15 ደቂቃ የእኛ ቁጥጥር ጥሩ ይመስል ነበር 2-0 እየመራን። በዛው የመቀጠል አቅም ነበረን። ግን ስህተቶች ተፈጥረዋል እነሱንም ወደ ጨዋታው አምጥተናቸዋል። ከዚያ በኋላ የነበረው ነገር ነጥብ ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ እንጂ የነበረንን የጨዋታ አካሄድ ለመጠበቅ ብዙም ጥሩ አልነበረም። ውጤቱን መያዙ እንዳለ ሆኖ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ አይተናል። ምክንያቱም ያገኘነውን ብልጫ አስጠብቀን መሄድ ሲገባን ከኃላም ከመሀልም የነበሩ ነገሮች የተበላሹ ነበሩ። በቀጣይ ጊዜ ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን። አሸንፈን መውጣታችን ለቀጣዩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለሙጂብ ቃሲም …

ሙጂብ እዛ አካባቢ ያለው ነገር በሙሉ ጥሩ ነው ፤ ምክንያቱም የጎል ሰው ነው። ልምምድ ላይም እንደዛው ነው ፤ ልምምድ ላይ የሚያደርጋቸውን ነገሬች እዚህም ያደርጋቸዋል። እንደውም ሦስት ብቻ አይደለም ቦታው ላይ እንደመገኘቱ አጥቃቀሙን የበለጠ ቢያስተካክል ኖሮ ደግሞ ደብል ሐት-ትሪክ መስራት የሚችልበት አቅም አለው። በጣም ተስፈኛ ነው። ወደፊትም ለሀገር ብዙ የሚጠቅም ነው። ብዙ ነገሮችን እያሻሻለ ይሄዳል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።

አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው…

በጨዋታው መስራት የፈለግነውን ነገር እየሰራን ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በተከላካይ አቋቋም ስህተት ሁለት ጎሎች ከተቆጠሩ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሙከራ አድርገናል ፤ ተሳክቶልን ሁለት ጎሎች አስቆጥረናል። ተጫዋቾቼ ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች አድርገዋል ብዬ አምናለው።

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ መደገም…

በፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት እና መደገም ሳይሆን ሊጋችን ላይ ለሁሉም ቡድን ዳኝነት እኩል ቢሆን ብዬ የግል አስተያየቴን እሰጣለሁ። በአዳማ ባሸነፍንበት ጨዋታም የዳኞች ስህተቶች ነበሩ። በየጨዋታው የዳኝነት ስህተት ዋጋ እያስከፈለን ነው። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ኑድኖችን በእኩል ዓይን ቢያይ ብዬ የግል አስተያየቴን እሰጣለሁ። ተጫዋቾቼ ማድረግ ያለባቸውን ነገር እያደረጉ ሳለ አላስፈላጊ ካርዶች ከጨዋታው ሪትም እንዲወጡ ያደረገበት ሂደት ስላለ ይታሰብበት ነው የምለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ