የሊግ ካምፓኒው የልዑክ ቡድን ከባህር ዳር ተመልሷል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚካሄድባት ሦስተኛ ከተማ የሆነችው ባህር ዳርን ሊገመግም ያመራው ቡድን ሥራውን አጠናቆ ተመልሷል።

ከመቼው ጊዜ በተሻለ በተቀናጀ እና በተሟላ ሁኔታ የዘንድሮውን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ሊግ ካምፓኒው እያስኬደ ይገኛል። የሁለት ከተሞችን ቆይታ አጠናቆ የሦስተኛ ከተማ ውድድርን እየተጠባበቀ የሚገኘው ሊግ ካምፓኒው በቅርቡ ወደ ባህር ዳር በማቅናት የልምምድ ሜዳዎች፣ የመጫወቻ ሜዳ፣ የኮቪድ ምርመራ ማዕከል፣ የሆቴል አቅርቦት እና የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታን ለመገምገም የልዑክ ቡድኑ ከሳምንት በፊት ወደ ስፍራው አቅንቶ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን ሰምተናል።

በአቶ ክፍሌ ሰይፉ (የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ) እና ዶ/ር ተገኔ ዋልተንጉስ (የሊግ ካምፓኒው የውድድር ሰብሳቢው) የተመራው ይህ የልዑክ ቡድን ባህር ዳር ከተማ በቆየበት ቀናት ውስጥ በሁሉም መልኩ ከተማዋ ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠው የተመለሱ መሆኑን ሰምተናል። ይሁን እንጂ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታየው የህክምና ቡድን እና የህክምና መስጫ ማዕከሉ መኪና ባህር ዳር ስታድየም ውስጥ የሚገኝበትን መንገድ ቢያጤኑት መልካም እንደሆነ ምክረ ሀሳብ መስጠታቸውን አውቀናል። የከተማው አስተዳደር የሚመጡትን እንግዶች በፍቅር ተቀብሎ በጥሩ መንስተንግዶ ለመሸኘት እና የከተማዋን በጎ ገፅታ ለማስተዋወቅ የተለየ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻላቸውንም ያገኘነው መረጃ ይገልፃል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከየካቲት አስራ ሦስት ጀምሮ ከ12ኛው እስከ 16ኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ ውድድሩን በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ