የአሠልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 0-0 ፋሲል ከነማ

ሱፐር ስፖርት ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኋላ ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ከጨዋታው በፊት ምክትላቸውን የቅድመ-ጨዋታ አስተያየት እንዲሰጡ ስለማድረጋቸው?

ሜዳ ውስጥ ለወጣቶች ዕድል ይሰጣል። በተመሳሳይ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ፣ ተስፋ ያላቸው እና መማር የሚፈልጉ አሠልኞችን የማብቃት ስራ ከእኛ ይጠበቃል። ስለዚህ ይሄንን ያደረኩት በእንደዚህ አይነት ትላልቅ ውድድሮች ላይ ራሱን መግለፅ እንዲችል እና ስለ ቡድኑ መናገር እንዲቸል ዕድል መስጠት ስለፈለኩኝ ብቻ ነው።

ስለ ጨዋታው?

በእንቅስቃሴው ደስተኛ ነበርኩ። ተጫዋቾቼ ለማሸነፍ የነበራቸው ፍላጎት ጥሩ ነበር። ነገርግን አመቱን ሙሉ ይዘነው የነበረውን የጨዋታ ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ተግብረውታል ማለት ያስቸግራል። ወጣቶች ስለነበሩ እና አሸንፈው መውጣት ስለፈለጉ ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት ይሄዱ ነበር። ከዚህ የተነሳ ኳሶች ሲቆራረጡብን ነበር። ይሄ ወደፊት የሚታረም ይሆናል። በተረፈ ግን ተተኪ ወጣቶች እንዳሉን ያሳየንበት መልካም አጋጣሚ ነበር።

ስለቀጣይ ዓመት ቆይታቸው?

ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ለጊዜው ውሌ እስኪያልቅ ድረስ ከሰበታ ጋር ነኝ። ካለቀ በኋላ ግን ማረፊያዬን በጊዜው አሳውቃለሁ።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ወደ ሜዳ ስላስገባቸው ወጣት ተጫዋቾች?

ወጣቶቹ ተጫዋቾቻችን ላይ ብዙ ተስፋ ነው ያየነው። ለሚቀጥለው ዓመት እነማን ጠንክረው ከእኛ ጋር ይቀጥላሉ የሚለውን ለማየት ዕድል አግኝተናል። በአጠቃላይ ወጣቶቹ ባለፈውም ሆነ ዛሬ ያሳዩት ብቃት ጥሩ ነው። ልምምድ ላይ የማቃቸውን ያህል ባይሆኑም ወደፊት ጨዋታ ሲያገኙ ይሻሻላሉ። ጥሩ ብቃት አላቸው። ጥሩም ተስፈኞች ናቸው።

ስለቻምፒየንስ ሊግ ዝግጅት?

ቡድናችን ዘንድሮ ያሳየው ብቃት እንዳለ ሆኖ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ማጠናከሪያ ለማድረግ ፍላጎት አለ። ለዚህም ውድድር ጥሩ ቅድመ ዝግጅት እናደርጋለን። ቢቻል ደግሞ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ቢገኙ መልካም ነው። እኔም በግሌ ጨዋታ ለማግኘት እየሞከርኩ ነው። ይሄ ቢሳካ መልካም ነው። ዞሮ ዞሮ በቻምፒየንስ ሊጉ ጥሩ ጉዞ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን።

ስለ ዋንጫው መታሰቢያነት?

ከምንም በላይ ከሁለት ዓመት በፊት በሞት ለተለየችኝ እናቴ እንዲሆን እፈልጋለሁ። እናቴ ለእኔ ብዙ ነገር ነች። በህይወቴ ትልቅ ድጋፍ በተለይ በስፖርቱ እንድቆይ ረድታኛለች እና ለእርሷ ክብር ይገባል። ከዚህ በተረፈ ሁሌም ከጎናችን ለሚሆኑት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች መታሰቢያ ይሁን እላለሁ። ዘንድሮ መልካም ውድድር አሳልፈናል። ለወደፊትም ጥሩ ነገር እንዲገጥመን እመኛለሁ።