ፋሲል ከነማ ሁለት ባለሙያዎችን ቀጥሯል

ትልልቅ ዝውውሮች ፈፅመው ቡድናቸውን ያጠናከሩት ዐፄዎቹ አሁን ደግሞ የአሰልጣኝ ቡድናቸውን ወደ ማጠናከር ገብተዋል።

የቀድሞ አሰልጣኛቸው ውበቱ አባተን መልሰው ካገኙ በኋላ በርከት ያሉ ወሳኝ ዝውውሮችን በመፈፀም ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ጠንክረው ለመቅረብ በሀዋሳ ከተማ ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በክለቡ ከነበሩ ረዳት አሰልጣኞች በተጨማሪ አንድ አሰልጣኝ ወደ ስብስባቸውን ሲቀላቅሉ የቪዲዮ ተንታኝ ባለሙያንም መቅጠራቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

ኤልመዲን መሐመድ የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ አባል ሆኗል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን ተገኝቶ በወንጂ ስኳር በይበልጥ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጥቂ ቦታ ላይ ተጫውቶ ያሳለፈው ኤልመዲን ኳስን ካቆመ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በማለት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ረዳት አሰልጣኝ እና በፕሮጀክቶች ደረጃም አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል። በቀጣይም ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ለመስራት ወደ ፋሲል አምርቷል።

ኤልሻዳይ ቤኬማ የፐርፎርማስ እና የቪዲዮ አናሊሲስት ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሯል። እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው እና በሀገራችን ኢትዮጵያ ባልተለመደው የቪዲዮ ትንተና ሙያ ብቅ ካለ በኋላ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ያለፉትን ዓመታት ሲያገለግል የነበረው ኤልሻዳይ በብሔራዊ ቡድን አብሯቸው ከሰራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በቀጣይም አብሮ ለማገልገል በፋሲል ከነማ የፐርፎርማንስ እና የቪዲዮ አናላይሲስት ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሯል።