ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ በመሻሻሉ ቀጥሎ በጊዜያዊነት ከወራጅ ቀጠናው ወጥቷል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ድሬደዋ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የወጣበትን ድል አስመዝግቧል።
አርባምንጭ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በቋሚ አስራ አንድ ውስጥ ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል ምንም የተጨዋች ለወጥ ሳያደርግ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማም ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ይዞ ከገባው ስብስብ ምንም የተጨዋች ለውጥ ሳያደርግ ነበር ለዛሬው ጨዋታ ወደ ሜዳ የገባው።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ነጥብ በግብ እዳ ተበላልጠው በወራጅ ቀጠናው ውስጥ በመቀመጥ የተገናኙበት ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎታል። ፌደራል ዳኛ ሚኬኤል አርአያም ጨሳታውን በጥሩ መንገድ መርቶ አጠናቋል።

የጨዋታው አጠቃላይ ገፅታ የተጠናቀቀው በመጀመርያ አጋማሽ ነበር። ድሬዳዋ ከተማዎች ከቆመ ኳስ ክዋሜ አትራም ካደረጋት ያልተሳካ የጎል ሙከራ በቀር ተጨማሪ ሙከራ ሳያደርጉ በወጡበት በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ጎል ፍለጋ ጫና መፍጠር የጀመሩት ገና በመጀመርያው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከርቀት በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን ኳስ ጀማል ጣሳው እንደምንም ያወጣውን የግቡ አግዳሚ ሲልሰው ተመስገን ካስትሮ አግኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረችውን ሙከራ በማድረግ ነበር። ከየትኛውም አቅጣጫ በሚነሱ ኳሶች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ እና ጫና በመፍጠር የድሬዳዋ ተከላካዮችን ሲፈትኑ የዋሉት አርባምንጮች በ6ኛው ደቂቃ አማኑኤል ጎበና በጥሩ መንገድ አሻግሮለት ፀጋዬ አበራ ከመሬት ጋር አንጥሮ የመታው ኳስ ለጥቂት የወጣበት አጋጣሚ የአርባምንጭ ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በዚህ ፈጣን እንቅስቃሴ የቀጠለው የአርባምንጭ አጨዋወት መዝለቅ የቻለው እስከ 20 ደቂቃ ድረስ ሲሆን ጎል እስካስቆጠሩበት ደቂቃ ድረስ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከነበረው ጥሩ እንቅስቃሴ እየወጡ መቀዛቀዝ አሳይተው ነበር ። ለመቀዛቀዙ እንደ ምክንያት ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ የጨዋታው እንቅስቃሴ በመሀል ሜዳ ላይ ብቻ መገደቡ እና የሁለቱም ቡድኖች ተጨዋቾች ለቡድን አጋሮቻቸው እርግጠኛ የሚሆኑ ኳሶችን አለማቀበላቸው ነው።

35ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጨዋታውን መልክ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ። በዕለቱ ተቀይሮ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ለአርባምንጭ አሸንፎ መውጣት ትልቁን ሚና ሲወጣ የዋለው ፀጋዬ አበራ ከሜዳው አጋማሽ የቀኝ መስመር ክፍል የተቀበለውን ኳስ ተከላካዮችን አልፎ ሳጥን ውስጥ በመግባት በነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው አለልኝ አዘነ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ አቀብሎት  አለልኝ ወደ ጎልነት በመቀየር አርባምንጭ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ድሬዳዋዎች የተሳካ የጎል ሙከራ አያድርጉ እንጂ  አናጋው ባደግ እና ወሰኑ ማዜን የቦታ ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እንዲሁም  የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾቹ ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ ዘላለም ኢሳያስ እና ኢማኑኤል ላሪያ በግላቸው ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የጎል እድል ሳይፈጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ በአዞዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ምንም ተጠቃሽ የጎል ሙከራ ሳይደረግበት መጠናቀቁ አስገራሚ ሆኖ አልፏል። አርባምንጭ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ምንም አይነት ፍላጎት ያላሳየበት ፤ ድሬዎችም የአጥቂ ቁጥር በመጨመራቸው እና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት መውሰዳቸው የጎል እድል ሳይፈጥርላቸው ቀርቷል።
ጨዋታው ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ በተደጋጋሚ  ኳስ አቀባዮች አርባምንጭ አሸንፎ እንዲወጣ ኳሱን ማዘግየታቸው የጨዋታው አካል እስኪመስል ድረስ በመደጋገሙ የዕለቱ ዳኛ ኳስ አቀባዮቹን ከሜዳ እንዲወጡ ያደረጉበት ውሳኔ የእለቱ አስገራሚ ክስተት ነበር።

አርባምንጭ ወደ ኋላ አፈግፍጎ መጫወቱ ድሬዎች በእንቅስቃሴ ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው እንዲቀርቡ ቢያደርጋቸውም ዘገምተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ዋጋ አስከፍሏቸው ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። በአርባምንጭ በኩልም ከጨዋታው አስቀድሞ እንደተሰጠው ግምት አሸንፎ ይውጣ እንጂ የሚቀር የቤት ስራ እንዳለ አመላክቶ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነበር።

ከአስከፊ ሳምንታት በኋላ ካለፉት 3 ጨዋታዎች 7 ነጥብ የሰበሰቡት አዲሱ አሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድኑን አርባምንጭ ከተማን ከወራጅ ቀጠናው በጊዜያዊነት በማውጣት ድንቅ ጅማሮ ሲያደርጉ ድሬዎች በአንፃሩ ለ10ኛ ተከታታይ ጨዋታ ድል ሳይቀናቸው በመውጣት በ15ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 


እዮብ ማለ – አርባምንጭ ከተማ

እንዳሰብነው አልተጫወትንም ከእረፍት በፊት የተሻልን ነበር በዚሁ አጋጣሚ ጎል አስቆጥረን ወተናል ልጆቹ ወደ አሸናፊነት ስነ ልቦና መመለሳቸው መልካም ነው በቀጣይ ጨዋታም ይህን ለማስቀጠል አጠናክረን እንሰራለን ። ይሁን እንጂ በመከላከል ላይ ያለን ጥንካሬ በአጥቂ መስመር ላይ ጎል የማስቆጠር ችግር አለብን በሁለተኛው ዙር ላይ ይህን ችግር ለማስተካከል የነቃ ተሳትፎ አድርገን ቡድኑን ለማጠናከር እንሰራለን ።


ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ከእረፍት በፊት የትኩረት ማጣት እንዲሁም የአየሩ ሁኔታ ተጫዋቾቼን ያስቸገራቸው ይመስለኛል። ከዚህ ባሻገር የመርሐ-ግብር አወጣጥ እና አካሄድ ለእኛ ከባድ ነበር ሀሙስ ተጫውተን ዛሬ መጫወታችን ያም ቢሆን ያሉትን ነገሮች ተቋቁመን ከእረፍት መልስ ተጭነን ለመጫወት ሞክረን ነበር ያም ሆነ ይህ ውጤቱ አስደሳች አልነበረም ቢሆንም ነገሮች ይቀጥላሉ እኛም ስራችንን እንሰራለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *