ሪፖርት | ንግድ ባንክ ጥሩ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ጎል በሀዲያ ሆሳዕና ተሸንፏል

ሪፖርት | ንግድ ባንክ ጥሩ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ጎል በሀዲያ ሆሳዕና ተሸንፏል

ነብሮቹ በጸጋአብ ግዛው የመጨረሻ ደቂቃ እጅግ ማራኪ ጎል ንግድ ባንክን 1ለ0 አሸንፈዋል።

ንግድ ባንኮች ከኤሌክትሪኩ የአቻ ውጤት ሱለይማን ሀሚድን በኪቲካ ጀማ ብቻ ሲተኩ ከመቻል ጋር 1ለ1 ባጠናቀቁት ሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ግን የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። ስንታየሁ ታምራት ፣ ሔኖክ አርፊጮ ፣ በየነ ባንጃው ፣ ሠመረ ሀፍታይ እና እዮብ አለማየሁ ወጥተው ያሬድ በቀለ ፣ ናትናኤል ሞገስ ፣ ብሩክ በየነ ፣ በረከት ወንድሙ እና ደስታ ዋሚሾ ተክተዋቸው በቋሚ አሰላለፍ የገቡ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ንግድ ባንኮች ከወራጅ ስጋት የሚያወጣቸውን ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት የምሽቱ መርሐግብር በፌዴራል ዳኛ ባህሩ ተካ መሪነት ተጀምሯል። ንግድ ባንኮች ተጭነው በመጫወት ይበልጥ የተጋጣሚያቸው የመጨረሻ ሜዳ ላይ በዋሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ በሽግግር ከመስመር ዋነኛ መነሻቸው በማድረግ ለመንቀሳቀስ ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም አደገኛ ሙከራዎች ደጋግመው ያገኙት ግን ከቆሙ ኳሶች ነበር። ኤፍሬም ታምራት ገና 6ኛው ደቂቃ ላይ አሻምቶ ካሌብ አማንኩዋ በግንባር ገጭቶ ዒላማዋን መጠበቅ ባልቻለችዋ ሙከራ የተጋጣሚያቸውን በር ያንኳኩት ሀምበራዊ ለባሾቹ በ28ኛው ደቂቃ ደግሞ ከቀኝ ሳይመን በረጅሙ ወደ ግራ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ በጥሩ ሽፋን በፍጥነት ዞሮ ወደ ግብ መቶ በተከላካይ ተጨርፋ ወደ ውጪ ወጥበታለች።

ከራሳቸው ሜዳ ኳስን ይዘው ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ በንግድ ባንክ ተጫዋቾች የሚቋረጥባቸው ነብሮቹ ወደ ፊት ከመሳብ ይልቅ በመከላከል የተጠመዱበት ነበር። ኤፍሬም ታምራት ከማዕዘን ካሻማ በኋላ አዲስ በግንባር ገጭቶ በላይኛው አግዳሚ ብረት ስትመለስ ፈቱዲን ያገኛትን ኳስ መጠቀም ያልቻሉት ንግድ ባንኮች ከቆሙ ኳሶች ያደርጓቸው የነበሩ ማጥቃቶች በማጠናከር በሌላ አጋጣሚ ኤፍሬም ከማዕዘን ለአዲስ ያደረሰውን አጥቂው በግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ የመከነበት ከደቂቃዎች መልስ ደግሞ ብሩክ በያሬድ የተያዘበት እንዲሁም ኤፍሬም አሁንም ከማዕዘን አሻምቶ ፈቱዲን ያገኛትን አጋጣሚ በአጋማሹ ያልተጠቀመባት የቡድኑን ጫና ከፍ ማለት ያመላከቱ ቢሆኑም አጋማሹ ግን ያለ ጎል ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ከቆመው ማጥቃታቸው የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በሳይመን ፒተር ፈጣን ጎል አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ በሚል ከተሻረች በኋላ ከመስመር በጥልቅ አጨዋወት አደጋ በሚፈጥር እንቅስቃሴ መሪ የሚሆኑበትን ጎል ለማስቆጠር የመጨረሻው ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ መድረስ ደርሰው ቢታዩም ያልተረጋጋው ማጥቃታቸው የተገኙ ዕድሎች ወደ ጎል መለወጥ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በመልሶ ማጥቃት ለመንቀሳቀስ ጥቂት ብቻ ጥረት ሲያደርጉ የሚስተዋሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ይበልጥ ሰዓት በተቃራኒው ሲያመራ በተጋጣሚያቸው በእጅጉ ተፈትነዋል። በ59ኛው ደቂቃ ከግራ አቅጣጫ ከእጅ ውርወራ ሳይመን ፒተር የሀድያን ተከላካዮች በረከት እና ዳግምን አልፎ ወደ ጎል ያደረጋት ሙከራ በግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ ስትመለስ በድጋሚ ሳይመን ቢያገኛትም በቀላሉ አምክኗታል።

78ኛው ደቂቃም ሱለይማን ከሳጥኑ ጫፍ ከሰነዘረው እና በያሬድ በቀለ ካከሸፈው ሙከራ መልስ በተጫዋች ቅያሪ ትኩስ ጉልበትን መያዝ የጀመሩት ነብሮቹ 81ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ተመስገን ብርሀኑ በተከላካዮች መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ጸጋአብ ግዛው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ የግራ ቋሚ ብረት ገጭታ ተመልሳለች። ጥሩ ፉክክሮችን በመጨረሻው አስር ደቂቃ በተመጣጠነ መልኩ እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች በሳይመን ፒተር እና ሱሌይማን ሀሚድ ካደረጉት ያለቀ ተከታታይ ሙከራ መልስ ግን በጭማሪው 90+3′ ላይ ብሩክ ማርቆስ ወደ ቀኝ የሰጠውን በጥሩ የእግር ስራ ተቀይሮ ከገባ ጀምሮ ተፅዕኖን ሲፈጥር የነበረው ጸጋአብ ግዛው በድንቅ ሁኔታ ፍሬው ጌታሁን መረብ ላይ በማሳረፍ በመጨረሻም በሀድያ ሆሳዕና 1ለ0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ከመጀመሪያ ደቂቃ አንስቶ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ባሰቡት መንገድ ማስኬድ መቻላቸው ጥሩ ጎን እንደነበር ገልፀው ተጭነው እንደ መጫወታቸው ማግባት ነበርን ካሉ በኋላ በመጨረሻም እግር ኳስ ስለሆነ ብቻ ለመሸነፍ መገደዳቸውን እና ትኩረታቸው ማግባት ላይ ብቻ ስለሆነ ክፍተትን በቡድናቸው እንደፈጠረ ተናግረዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በበኩላቸው በማጥቃትም በመከላከልም በደንብ ተጋጣሚያቸውን መፈተናቸውን ጠቁመው ጥሩ ባይባልም መጥፎ ጨዋታ እንዳልነበር በመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚ መበለጣቸውን ያንንም እንዳልተቆጣጠሩ ከተናገሩ በኋላ በሁለተኛ አጋማሽ በቅያሪ ተጫዋቾች እገዛ የሚፈለገውን ውጤት ይዘው እንዲወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።