መረጃዎች | 18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | 18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

18ኛ ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይደረጋል። ጨዋታዎቹን  የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና

በመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ ተለያይተው በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በስድስቱም ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ግብ ያላስቆጠረው የማጥቃት አቅማቸው እጅግ አሳሳቢ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አራት ግቦች ተቆጥረውባቸው አሰቃቂ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ  በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው መውጣታቸው ግን የተከላካይ መስመራቸውን መሻሻል የሚያሳይ ጉዳይ ሆኖ ይጠቀሳል። ባደረጓቸው 17 የሊጉ ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስቆጥረው 17 ግቦችን ያስተናገዱት ብርቱካናማዎቹ 20 ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከናፈቃቸው ሦስት ነጥብ ጋር ለመታረቅና ደረጃቸውን ለማሻሻል በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

ሦስት ተከታታይ ድሎችን ከተቀዳጁ በኋላ በሲዳማ ተሸንፈው ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርተው ሽረ ምድረገነትን አሸነፈው ዳግም ወደ ድል ከተመለሱ በኋላ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ዛሬ በነጥብ ከሚስተካከላቸው ድሬዳዋ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል። 15 ግቦችን አስቆጥረው 17 ግቦችን (በአማካይ በጨዋታ አንድ) ያስተናገዱት ነብሮቹ የተቆጠረባቸውን ያክል ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ ሲሆን ተከላካይ መስመሩን አጠናክረው እንዲሁም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን የተሻለ በማድረግ አሸንፈው ደረጃቸውን ለማሻሻል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ከተማ አስቻለው ታመነ እና ሬድዋን ሸረፋን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ሲሰማ አቤል አሰበ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና አብዲሳ ጀማል ከጉዳት ባለማገገማቸው እንዲሁም ሄኖክ ሀሰን ቅጣት ባለመጨረሱ ግልጋሎት አይሰጡም። ሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ቡድኖቹ በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ነብሮቹ 5 ሲያሸንፉ ብርቱካናማዎቹ 4 ጊዜ ድል አድርገው በ3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። 31 ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነት ሀዲያ ሆሳዕና 17 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 14 ጎሎች አስቆጥረዋል።

መቻል ከሸገር ከተማ

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ድል በማድረግ በመሪዎቹ አንገት ስር የገባው እና በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው መቻል በመጨረሻው ጨዋታ መድን ላይ አንድ ግብ ብቻ ያስቆጥር እንጂ በሌሎች ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ግቦችን እያስቆጠረ ተጋጣሚውን ማሸነፉ የቡድኑን የፊት መስመር ጥንካሬ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዱ ቡድኑ ከፊት ከኋላም በደንብ የተገነባ እና በመከላከሉም በማጥቃቱም ጥሩ መሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከመሪው በአራት ነጥብ ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከመቀመጡ አኳያ ከፊቱ ያለውን ጨዋታ አሸንፎ ተፎካካሪነቱን ይበልጥ ማጠናከር ስለሚጠበቅበት የዛሬውን ጨዋታ እንደቀላል እንደማይመለከተውና አሸንፎ የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ የሚገባም ይሆናል።

9ኛ ሳምንት ላይ ባህርዳር ከተማን ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ ካሸነፉ በኋላ የሜዳ ለውጥ አድርገው ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት የተሳናቸው ሸገር ከተማዎች ሳይጠበቁ ወደ ታች እየወረዱ በመሆኑ የዛሬውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለባቸው። ምንም እንኳን በመጨረሻዎች ስድስት ሳምንታት ከሲዳማ ቡና ጋር ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ አምስቱን ጨዋታ በአቻ ውጤት ቢያጠናቅቁም በሁለት ጨዋታ ብቻ አንድ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው። በ17 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ የማያሸንፍ ከሆነ በመጀመሪያው ዙር ራሱን በወራጅ ቀጠና ውስጥ ስለሚያስገኘው የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ በሙሉ ኃይል ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

መቻል ከውብሸት ጭላሎ እና ኮሊንስ ኮፊ በተጨማሪ ዩሐንስ መንግስቱ እና አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት ምክንያት እንደሚያጣ ታውቋል። ሸገር ከተማ በዛሬው ጨዋታ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱም ቡድኖች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ሲዳማ ቡና  ከባህር ዳር ከተማ

ላለፉት 13 ሳምንታት ሽንፈት ሳያስተናግዱ ቆይተው ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ ግብ በነጌሌ አርሲ የዓመቱን ሁለተኛ ሽንፈት ያስተናገዱት የወቅቱ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት አሸንፈው ሁለት አቻ በመውጣት ማግኘት ካለባቸው 18 ነጥብ 11 አሳክተዋል። በሊጉ ልምድ ያላቸውን የተከላካይ መስመር በመያዙ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ሁለት ግብ ከማስተናገዱ ውጪ ብዙም ግብ አለማስተናገዱ የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ማሳያ ነው። ለረጅም ሳምንታት በነጥብ ልዩነት ሊጉን እየመራ የቆየው ቡድኑ አሁን ተከታዮቹ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ልዩነቱን በማጥበባቸው ምክንያት የዛሬውን ጨዋታ አሽንፎ መሪነቱን ማጠናከር ግድ ይለዋል።

በ14ኛው ሳምንት መቻልን አሸንፈው ከተከታታይ አቻ ውጤት በኋላ ወደ ድል መመለስ የቻሉትና ያለፉትን ሦስት ሳምንታት ምን ግብ ሳያስቆጥሩ እንዲሁም ሳይቆጠርባቸው ተከታታይ አቻ ያስመዘገቡት ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸው የኋላ ደጀናቸው ጥንካሬ ተደርጎ ቢወሰድም ሁለት ግብ ብቻ ማስቆጠራቸው የማጥቃት ኃይላቸው ግብ ከማስቆጠር ብዙ እንደራቀ ያመላክታል። ባሳለፍነው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጥሩ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ቢሆንም የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ላይ ደካማ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ እንደ ተከላካይ መስመራቸው ሁሉ አሁንም ማጥቃት ላይ ያለውን ችግር ቀርፈው ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት በማሸነፍ ወኔ ወደሜዳ መግባት ይኖርባቸዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ሆኖም ግን ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት የዛሬው ጨዋታ ያመልጠዋል።

ባህር ዳር ከተማ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ክንዱ ባየልኝን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄን ደግሞ በቅጣት ምክንያት የሚያጣ ይሆናል።

ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በ12 የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ ሲዳማ ቡና 6 ባህርዳር ከተማ ደግሞ 4 ጨዋታዎች ሲያሸንፉ 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ሲዳማ 18 ባህር ዳር ደግሞ 14 ግቦች አስቆጥረዋል።