የብሄራዊ ቡድኑ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን ትላንት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በብሄራዊ ቡድኑ የህክምና እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ማብራርያ ዋና ዋና ሃሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
-“የቡድኑ ተጫዋቾች ከውድድር ነው የመጡት፡፡ ከረጅም ውድድር ስለመጡ የመጀመርያ ስራችን የነበረው ብቃታቸውን መፈትሽ ነበር፡፡ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ያደረገው የምርጫ ጨዋታ ወቅታዊ የአካል ብቃት ደረጃቸውን ለማወቅ እጅግ ጠቅሞናል፡፡ የተጎዱ ፣ ቶሎ የሚያገግሙ እና ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ብቁ የሆኑትን የለየነው በዚህ የምርጫ ጨዋታ ነው፡፡”
-“ባህርዳር ካረፍን ጊዜ ጀምሮ እየተደረግልን ባለው ነገር ሁሉ ደስተኞች ነን፡፡ ምግቦቹ እና ምኝታው ለተጫዋቾቻችን በምንፈልገው መልኩ ቀርቦልናል፡፡”
-“አዳዲስ እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቅልቅል በመሆኑ በስነልናው በኩል መሰራት የሚገባቸውን ስራዎች ሰርተናል፡፡”
-“ጀማል ኳስ ለመያዝ ሲወረወር በትከሻው መሬት ላይ በማረፉ ቀኝ እጁ ላይ የውልቃት ጉዳት አጋጥሞታል፡፡ ለቀጣዮቹ 2 ሳምታትም ከሜዳ ይርቃል፡፡ ኤፍሬም አሻሞ ደግሞ ከክለቡ ይዞተ የመጣው ጉዳት አገርሽቶበት ነው እንዲያርፍ ያደረግነው፡፡ ለነገው ጨዋታ ብቁ ስለማይሆን እንጂ ጤናው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡”