ሪፖርት | አዳማ ከተማ በሜዳው በአይበገሬነቱ ቀጥሏል

በ21ኛ ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 1-0 በማሸነፈ በሜዳው አይበገሬነቱን አስቀጥሎ ወጥቷል።

አዳማ ከተማ በ20ኛ ሳምንት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሀዋሳ ከተማ የ2-1 ሽንፈት አስተናግዶ ከተመለሰው ስብስቡ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ እና አምበሉ ሱሌይማን መሀመድን በጉዳት እንዲሁም ደሳለኝ ደባሽን አሳርፎ በምትኩ ጃፋር ደሊል ፣ ኢስማኤል ሳንጋሪ እና ዳዋ ሆቴሳን በመያዝ ወደ ሜዳ ሲገባ በድሬዳዋ በኩል በ19ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከደደቢት ጋር ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተለያየበት ስብስብ ውስጥ አህመድ ረሺድ ፣ ዮሴፍ ዳሙዬ እና ያሬድ ታደሰን አሳርፎ በምትኩ ወሰኑ ማዜ ፣ ዮሴፍ ደንገቶ እና ሚካኤል አኩፎን በማካተት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ፌዴራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በሚገባ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ በመራበት በዚህ ጨዋታ የጎል ሙከራ መመልከት የጀመርነው ገና በ3ኛው ደቂቃ በእንግዶቹ ድሬዎች አማካኝነት ሲሆን ወሰኑ ማዜ የጣለለትን ኳሰ በረከት ይስሀቅ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጃፋር ደሊል ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ኳሷን ቺፕ አድርጎ ለማስቆጠር ሲሞክር በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ጨዋታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋግሎ ቀጥሎ 7ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ህንፃ ኳሱን ይዞ ወደ ጎል ሰብሮ ብቻውን በመግባት ከሳምሶን አሰፋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ለማለፍ ሲሞክር ኳሱ ረዝሞበት ወደ ውጭ የወጣበት በአዳማ በኩለ የመጀመርያው ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።

ድሬዎች በተሻለ ሁኔታ በተንቀሳቀሱበት የመጀመርያው አጋማሽ 9ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ከ16:50 ውጭ ሀብታሙ ወልዴ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ጃፋር ደሊል እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ብዙም ሳይቆይ አዳማዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በረከት ደስታ ከከነዓን ማርክነህ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ከመሬት ጋር አንጥሮ ቢመታውም በግቡ ቋሚ ታኮ ለጥቂት ወግቶበታል። ድሬዎች በጨዋታ እንቅስቃሴ እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት ግልፅ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በዕለቱ ኳሶችን ሲያመክን የዋለው በረከት ይስሀቅ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል። በረከት 16ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ከአማካዮቹ የተቀበለውን ኳስ በቀኝ እግሩ መታው ተብሎ ሲጠበቅ ሱሌማን ሰሚድን አሸማቆ በማለፍ ሌላ ነፃ ኳስ ፈጥሮ ወደ ጎል መታው ተብሎ ሲጠበሽ በድጋሚ ተጨዋች ለማለፍ ሲያስብ ተከላካዮች ተረባርበው ኳሱን አክሽፈው ሊወጡበት ችለዋል። በ8 የመከላከል ባህሪ ባላቸው ተጨዋቾች በራሱ የሜዳ ክፍል አመዝኖ ለሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማ በ15 ደቂቃ ውስጥ የተገኙ 3 የጎል አጋጣሚዎችን አለመጠቀማቸው የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

በጨዋታ ቀስ በቀስ ኳሱን መቆጣጠር የቻሉት አዳማዎች በ23ኛው ደቂቃ ኢስማኤል ሳንጋሪ ፣ ከንአን ማርክነህ  እና ዳዋ ኡቴሳ ተቀባብለው በመጨረሻም ኳሱን ተቀብሎ ወደ ሳጥን የገባው አንዳርጋቸው ይላቅ ያሻገረውን አዲስ ህንፃ በግንባሩ ገጭቶ ሳምሶን አሰፋ መረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። 

ከጎሉ መቆጠር በኋላ የተቀዛቀዙት እንግዶቹ  ድሬዎች በአዳማ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲሆን በ30ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ በቅጣት ምት የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ሳምሶን አሰፋ ያዳነበት እና ከነዓን ማርክነህ 32ኛው ደቂቃ ላይ ብቻውን ከሳምሶን አሰፋ ጋር ተገናኝቶ በቺፕ ለማስቆጠር ሲሞክር ለጥቂት የወጣበት ሙከራዎች የጎል መጠናቸውን ሊያሰፉ የሚችሉባቸው ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ከተደረገው የጎል ሙከራ ይልቅ የተጨዋች ቅያሪ የበዛበት እና ብዙም ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ ያልተመለከትንበት ነበር። በረከት ሳሙኤል በሰራበት ጥፋት በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ዳዋ ኡቴሳን በመተካት ተቀይሮ የገባው ፍርድአወቅ ሲሳይ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችል በተለይ 53ኛው ደቂቃ ላይ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ ቆርጦ በመግባት በጥሩ ሁኔታ መትቶ በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የሚጠቀስ ነበር። 
አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ የአቻነት ጎል ፍለጋ የተከላካይ አማካዮችን ቁጥር በመቀነስ ያሬድ ታደሰን ቀይረው ካስገቡበት ሰአት አንስቶ በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመቅረብ ጥረት ቢያደርጉም የአዳማን ጠንካራ የመከላከል አቅም ሰብረው ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። ሆኖም የፊት አጥቂው በረከት ይስሐቅ ከውሳኔ ችግር በ68ኛው ደቂቃ ሌላ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀም የቀረበት ሙከራ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። 

አዳማዎች ተጨማሪ ጎል ከማስቆጠር ይልቅ በጥንቃቄ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት በማሰብ ሱራፌል ዳኛቸው እና ኤፍሬም ዘካርያስን ቀይሮ በማስገባት ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት የተከተሉት ታክቲክ ሲሳካ በአንፃሩ ድሬዎች ያደረጉት የተጨዋች ቅያሪ ለውጡ የቡድኑን እንቅስቃሴ ቢያሻሽለውም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ በሜዳው ከተሸነፈ 30 ጨዋታዎች እና 726 ቀናትን ያስቆጠረው አዳማ ከተማ ደረጃውን በማሻሻል 5ኛ ላይ ሲቀመጥ በተቃራኒው ከሜዳው ውጪ ካሸነፈ አንድ አመት ያለፈው ድሬዳዋ ከተማ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። 

የአሰልጣኞች አስተያየት

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ 

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሆኖም ባሰብነው መልኩ መጫወት አልቻልንም። ቡድናችንን የተጫዋቾት ጉዳት በተደጋጋሚ እየፈተነው ይገኛል። ያም ቢሆን ባልተሟላ ስብስብ ፈጣሪ ሦስት ነጥብ አልከለከለንም፤ ጨዋታውን ተቆጣጥረን አሸንፈን ወጥተናል። እንቅስቃሴያችን ከባለፈው የተሻለ ነበር ፤ ነገር ግን የሚቀረን ነገር አለ። ከጉዳት ተጨዋቾች ሲመለሱ ጥንካሬያችን ይመለሳል ።  

ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ 

በእግርኳስ መጀመርያ ላይ ያገኘሀቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ካልቻልክ መጨረሻ ላይ እንደ ዛሬው ዋጋ ከፍለህ ትወጣለህ። በአንድ ጊዜ መጥተው ጎል አስቆጠሩ። ከዛ በኋላ ተከላከላክለው ውጤት አስጠብቀው ወጥተዋል። ይህም ቢሆን በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻልን ነበርን ። 

ከሜዳችን ውጭ አሸንፎ መውጣት ተቸግረናል ። ከሜዳ ውጭ ስትጫወት ብዙ ችግሮች አሉ ፤ በዳኝነት በኩል መቋቋም ካልቻልክ ብዙ ውጤት ታጣለህ። ዳኞች ስጋት ውስጥ ሆነው ነው የሚያጫውቱት። ዛሬ በዳኝነት በኩል ደስተኛ አልነበርኩም።