ሪፖርት | ብሩክ በየነ ሀዋሳን ታድጓል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛው ሳምንት ሀዋሳ በሜዳው ለረጅም ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር በተጫወተው ጅማ አባ ጅፋር ተፈትኖ በብሩክ በየነ ብቸኛ ጎል 1ለ0 አሸንፏል፡፡

ሀዋሳዎች ባለፈው ሳምንት መቐለ ላይ በሽረ በተረቱበት ወቅት ይዘውት የገቡት የመጀመርያ አስራአንድ ላይ ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ አባጅፋሮች በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ ሱራፌል ዐወል እና ወንድማገኝ ማርቆስ ወደ ተጠባባቂ ወርደው ኤልያስ አታሮ እና ሄኖክ ገምቴሳ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረውታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ በስታዲየሙ ውስጥ ተገኝተው በተከታተሉት ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፍፁም ለዕይታ ማራኪ ያልሆነ እና የወረደ እንቅስቃሴን የተመለከትንበት ነበር፡፡ ለአስራ አምስት ያህል ደቂቃዎችም ቡድኖቹ ምንም ለማጥቃት ትጋት ሲያደርጉ ያላየን ሲሆን ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ የመሻሻል ነገሮች ይታያሉ ተብሎ ቢጠበቅም በዛው የቀጠለበት ነበር፡፡

በ10ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች በግራ በኩል በያኦ ኦሊቨር በተገኘች አጋጣሚ ተጫዋቹ ወደ ግብ ሲያሻማ ሄኖክ አየለ አመቻችቶ በሚገባ የሰጠውን ብሩክ በየነ ወደ ግብ መቷት ሰዒድ ሀብታሙ የያዛት ኳስ የመጀመሪያዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች። ጅማዎች ከማጥቃት የተቆጠበ የሚመስል አጨዋወትን ቢከተሉም አጥቂው ብዙዓየው እንደሻው በግሉ ሲታትር የነበረበት መንገድ ደግሞ አስደናቂ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተጫዋቹ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሊረዱት የሚችሉ አጋዥ ተጫዋቾች ባለመኖራቸው ተጫዋቹ ሲባክን ተስተውሏል፡፡

26ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ የተከላካይ አማካይ አብርሀም ታምራት ከሀዋሳው አማካይ ዘላለም ኢሳይያስ ጋር መሀል ሜዳው ላይ ኳስን ለማግኘት በሚታገሉበት ወቅት አስቀድሞ ቢጫ ካርድ የተመለከተው አብርሀም ሆን ብሎ ተማቷል በሚል የእለቱ ዳኛ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደውታል፡፡

ቀሪውን ስልሳ አራት ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት ጅማዎች በቀላሉ ሀዋሳዎች ብልጫን ይወስዱባቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም የተባለውን ሁሉ ፉርሽ ያደረገ እንቅስቃሴን ተግባራዊ በማድረግ የተከላካያቸውን ቁጥር አሳድገው መከላከልን ምርጫቸው ለማድረግ ተገደዋል፡፡ 38ኛው ደቂቃ ብዙአየው እንዳሻው ከቅጣት ምት ከርቀት አክርሮ መቶ ቢሊንጌ ኢኖህ በሚገርም ብቃት ከግቡ ጠርዝ ላይ አወጣት እንጂ መሪ ሊሆኑም ተቃርበው ነበር።

ሀዋሳዎች በበኩላቸው 41ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ መሀል ለመሀል አሾልኮ ሰጥቶት ሄኖክ አየለ በቀጥታ መትቶ ጅማዎች አንድ ነጥብ ይዘው እንዲሄዱ ብልጠቶችን በጊዜ ሲጠቀም የነበረው ሰዒድ ሀብታሙ እንደምንም አውጥቶበታል፡፡ብዙም ሳቢ ያልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ጎል ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀዘቀዘ እና አሰልቺነቱ ሳይለወጥ ተባብሶ በቀጠለበት ጨዋታ የእለቱ ዳኛ አዳነ ወርቁ ላይ የጅማ አባጅፋር አሰልጣኞች ተደጋጋሚ ቅሬታን ከሚገልፁበት ስሜታዊ እንቅስቃሴዎች ውጪ ሜዳ ላይ የሁለቱን ቡድኖች አጨዋወት ልንረዳ ያልቻልንበት ነበር፡፡ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ይህ አጋማሽ ጅማዎች ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት በብዙዓየው ለመጫወት የሞከሩበት፤ ሀዋሳዎች ቀዳዳን ፈልጎ ለማስቆጠር የጣሩበት ነበር፡፡

60ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከሄኖክ ድልቢ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዘው ገብተው አለልኝ ለብሩክ ሰቶት ብሩክም ተረጋግቶ ማስቆጠር እያቻለ ወደ ላይ ሰዷታል፡፡ 74ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጅማ አባጅፋርን የተከላካይ ክፍል መዘናጋት ተመልክቶ አክሊሉ ተፈራ መሀል ለመሀል አሾልኮ ለብሩክ በየነ ሰቶት ልማደኛው አጥቂ ሰዒድ ሀብታሙን ሁሉ አልፎ በግራ በኩል በድንቅ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል። ከግቧ በፊት የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ላይ ተቃውሞን እያሰሙ የነበረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ አሰልጣኝ አዲሴ ግቧ ስትቆጠር ወደ ደጋፊው በመዞር ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ ደስታቸውን የገለፁበት ስሜት አስገራሚ ነበር፡፡

ጅማ አባጅፋሮች በጎዶሎ ተጫዋች እየተጫወቱ ከመሆኑ አንፃር በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሆነው የታዩ ሲሆን እጅግ አስቆጪ ዕድሎችን አግኝተውም በቀላሉ አምክነውታል፡፡ ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉም ሁለት ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝቶ አምክኗቸዋል። በተለይ 89ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ በግራ በኩል አሻግሮ ኤርሚያስ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ምናልባትም ጅማን አቻ የምታደርግ እድል ነበረች፡፡ 
መደበኛ ደቂቃው ተጠናቆ የተሰጠው አራት ጭማሪም ሊፈፀም ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ብዙዓየው እንዳሻው ኳስ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል እየነዳ ሲገባ በሀዋሳ ተከላካዮች ተጠልፎ ወድቆ የእለቱ ዳኛ ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጡ አልፈዋል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞን ከቡድኑ ተጫዋቾች ያስተናገዱ ሲሆን የጅማ ተጫዋቾች ዳኛውን በመክበብ ያላቸውን ቅሬታ ያሰሙበት መንገድ ዳኛው በተከታታይ ለሦስት ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ እንዲመዙ አድርጓቸዋል፡፡ ጨዋታውም ብሩክ በየነ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በሀዋሳ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ