ሪፖርት | ባህር ዳር ሲዳማን ረቷል

በመጀመሪያው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

በጨዋታው መጀመሪያ የተሻለ ንቃት ያሳዩት ባህር ዳር ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። 5ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ የሲዳማ ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው ጎል አፋፍ ስር ያላራቁትን ኳስ ተጠቅሞ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂውን በማለፍ ጭምር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ኳስ ተቆጣጥረው ክፍተቶችን ይፈልጉ የነበሩት ሲዳማዎች የአቻነት ግቡን ከማግኘታቸው ይልቅ ለመልሶ መጠቃት መጋለጣቸው ብሶ ይታይ ነበር። ቅብብሎቻቸው ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሳይደርሱ ይቋረጡ ስለነበር ሙከራዎቻቸው ከሳጥን ውጪ የሚደረጉ እና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሆነው ነበር። የባህር ዳሮች የሳምሶን ጥላሁን እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙ የአማካይ ጥምረትም የሲዳማ የልብ ምት የሆነውን ዳዊት ተፈራን መቆጣጠር አልከበደውም። ኳስ ነጥቀው የሚሰነዝሩት ጥቃትም የጣና ሞገዶቹን አስፈሪ አድርጓቸዋል። በተለይም 15ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከዜናው ፈረደ ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ የሞከረው እና ግብ ጠባቂው ያወጣበት ሙከራ የባህር ዳር መልሶ ማጥቃትን ፍንጭ የሚሰጥ ነበር።

ሲዳማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው በዳዊት ሞክረውት ማናፍ ዐወል ከተደረበበት ኳስ በኋላ ግን ከኋላ የሚተዉት ክፍተት ለሁለተኛ ግብ ዳርጓቸዋል። በዚህም 16ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከባዬ የደረሰውን ድንቅ ኳስ ተጠቅሞ ክፍሌ ኪአን እንዲሁም በድጋሚ መሳይ አያኖን በማለፍ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላ ግን የባህር ዳር የመልሶ ማጥቃት ፍጥነት እየቀነሰ የሲዳማ የኳስ ቁጥጥር ከፍ እያለ መጥቷል። በእርግጥ ሲዳማዎች የተሻሉ ሆነው ከመጡባቸው ደቂቃዎች ከረጅም ርቀት ሙከራዎች ውጪ ጠንካራ የሳጥን ውስጥ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል። የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ ግን ሦስቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ላይ የቦታ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ከባባድ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። 36ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ በተከታታይ ያረጓቸው ጠንካራ ሙከራዎች ግብ ላለመሆን የሀሪሰን ሄሱን ጥረት ጠይቀዋል። ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ሊያመሩ ሲሉም የዳዊት ተፈራ ቅጣት ምት ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣው።

ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድናቸውን አሸጋሽገው ያስር ሙገርዋን ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ በማሰለፍ የአበባየሁ ዮሐንስ እና ግሩም አሰፋን የማጥቃት ተሳትፎ በመጨመር የቡድናቸው የኳስ ቁጥጥር ፍሬ እንዲያፈራ ጥረት አድርገዋል። ያም ቢሆን ባህር ዳሮች ቡድኑ ከኋላ የሚተወውን ክፍተት ካመጠቀም አልቦዘኑም። ምንም እንኳን ቁልፍ ተጫዋቻቸው ፍፁም ዓለሙን በጉዳት ቢያጡም በእሱ እግር የተተካው ሄኖክ አወቀ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ 50ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም አድርጎ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ሲዳማች ቅብብላቸው ሰምሮ ሳጥን ውስጥ በተገኙበት አጋጣሚ ደግሞ ይገዙ ከዳዊት ተቀብሎ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለባቸው ተከታዮቹ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ሚካኤል ሀሲሳን በአበባየው ቦታ በማስገባት በድጋሚ የአማካይ ክፍላቸውን አድሰዋል። ነገር ግን ያለመጣን ከግቡ የሚርቀው የኋላ ክፍላቸው አደጋ አላጣውም። 59ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ከመናፍ የተቀበለውን ኳስ ይዞ ረጅም ርቀት ገፍቶ ሳጥን ውስጥ በመግባት እና ግርማ በቀለን በማለፍ ለዜናው ፈረደ ያመቻቸው ኳስ ለጥቂት ነበር ጎል ከመሆን የዳነው። በዜናው የተተካው ወሰኑ ዓሊም 72 ኛው ደቂቃ ላይ የመሳይ አይኖን ረጅም ኳስ ተደርቦ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ አግዳሚ ነበር የተመለሰበት። በዚህ መንገድ ሙከራዎችን ያስተናገዱት ሲዳማዎች ኳስ ይዘው የመጫወት ሙከራቸውን ቢቀጥሉም። በጨዋታው ማብቂያ ላይ ከግራ መስመር ተሻምቶ በመናፍ ዓወል በእጅ የተናካን ኳስ ተከትሎ በዳዊት ተፈራ አማካይነት የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ከማስቆጠራቸው ውጪ ውጤቱን ማጥበብ ሳይችሉ 3-1 በሆነ ውጤት ተረተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ