ድሬዳዋ ተጨማሪ ጨዋታዎችን ታስተናግዳለች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት የሁለት ሳምንት መርሐግብሮች በድሬዳዋ ተጨምረዋል፡፡

የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በባህር ዳር ከተማ የአምስት ሳምንታት ቆይታን ካደረገ በኋላ በድሬዳዋ እንደቀጠለ ይታወሳል፡፡ ሰባተኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ በድሬዳዋ በጣለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የተነሳ ጥቂት ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ሲሆን አሁን ላይም ውድድሩ ዘጠነኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ ደርሷል፡፡

ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ አስረኛ ሳምንት ድረስ ቀደም ብሎ በወጣው መርሀግብር መሠረት የማስተናገድ ሚናውን የተረከበችው ድሬዳዋ ቀጣይ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎችን እንድታስተናግድ መመረጧን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች፡፡

በዚህም መሠረት ተጨማሪ የሁለት ሳምንት መርሀግብሮች ውድድሩ ወደ አዳማ ከመሄዱ በፊት እንድታስተናግድ በአክሲዮን ማህበሩ ተጨማሪ ዕድልን ያገኘች ሲሆን በሰባተኛው ሳምንት በዝናብ ምክንያት የተቋረጡን ጨምሮ በከተማዋ እንደሚደረግ ተሰምቷል፡፡

በዓለም ዋንጫ ምክንያት የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትን እያገኘ የማይገኘው ውድድሩ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ለዋልያዎቹ ዝግጅት እና ለውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ በአዳማ ሲቀጥል የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭቱ ዳግም እንደሚጀምርም ሰምተናል፡፡