ድሬዳዋ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች እንዲሁም ሸገር ከተማ ከዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ በማሸነፍ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ፍፁም የሚባል ብልጫን መውሰድ ችለዋል። የሜዳው የመሃል ክፍል ላይ ብልጫዎችን በመውሰድ በርካታ የግብ አደጋዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን 27ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ታደሰ ከመሐመድኑር ናስር ተቀብሎ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰ ሲሆን ያንኑ የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ መሐመድኑር ናስር ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ኦውሱ አንድሪውስ መልሶበታል። እንዲሁም 32ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱልሰላም የሱፍ የቅጣት ምት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂውን ማለፍ ተስኖት አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሀድያ ሆሳዕናዎች ራሳቸውን አሻሽለው በመቅረብ ብልጫዎችን መውሰድ የቻሉ ሲሆን ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ ከ10 ደቂቃዎች በላይ መዝለቅ አልቻለም። 64ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰላም የሱፍ ከመስመር ወደ ሳጥን ያቀበለውን ኳስ መሐመድኑር ናስር ወደ ግብነት ቀይሮ ብርቱካናማ ለባሾቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

አሁንም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫናዎችን ፈጥረው መጫዎታቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያው ተጫዋች ሄኖክ አርፊጮ ለግብ ጠባቂው በግንባር ለማቀበል የሞከረው ኳስ ማጠሩን ተከትሎ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ግብ ጠባቂውን በማለፍ በጨዋታው ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል። መሐመድኑር ናስር 77ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ገጭቶ ቋሚ በመለሰበት እና 90ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው እንደምንም ብሎ ባወጣበት ሙከራ ሀትሪክ ሚሰራበትን ዕድል ቢፈጥርም ተጨማሪ ግቦችን ግን ሳንመለከት ጨዋታው በድሬዳዋ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቻል ከ ሸገር ከተማ
ከድል እና ነጥብ መጋራት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ መቻሎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በተቃራኒው ሸገር ከተማዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዛ ብለው ጥንቃቄ የተሞላበት ጥብቅ የሆነ የመከላከል አጥር በመስራት የመቻልን የማጥቃት ሙከራዎች መመከት ችለዋል። በአጋማሹ የሸገር ከተማዎቹ የፍቅሩ አለማየሁ የግንባር እና ከቡልቻ ሹራ ደካማ የሆነ የርቀት ኳስ ሙከራዎች በስተቀር የግብ ሙከራዎችን ሳንመለከት አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በነበራቸው የአጨዋወት ስልት የተመለሱ ሲሆን 59ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በዛ ብለው በሄዱበት አጋጣሚ ሸገር ከተማዎች ኳስን በመንጠቅ በመልሶ ማጥቃት ይዘውት የመጡትን ኳስ የሜዳው አካፋይ ላይ ወጣቱ ተጫዋች ዳዊት ካሳው መሬት ለመሬት ሰንጥቆ ያቀበለው ሲሆን ቡልቻ ሹራ ድንቅ በሆነ ሩጫ ግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በውድድር አመቱ የሊጉን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል።
መቻሎች በበኩላቸው የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ከሽንፈት የሚታደጋቸውን ግብ ለማግኘት ጫናዎችን ፈጥረው ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጠንካራውን እና በጥሩ መሰረት የተገነባውን የሸገርን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ሸገር ከተማዎች ከተከታታይ ዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ በቡልቻ ሹራ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከናፈቁት ድል ጋር ታርቀዋል።

