ዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዟቸውን በሽንፈት ደምድመዋል

በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታ ግብፅን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1-0 ተሸንፏል

በመጪው ጥር አይቮሪኮስት ላይ የሚከናወነው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎችን የሚለየው ማጣሪያ ከዓመት በፊት መጀመሩ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ ‘መ’ ተደልድሎ ጨዋታዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ምንም እንኳን ብሔራዊ ቡድኑ ቀደም ብሎ ለውድድሩ አለማለፉን ቢያረጋግጥም ዛሬ ምሽት 01:00 ላይ በመጨረሻ ጨዋታው የግብፅ አቻውን በጁን 30 ስታዲየም ገጥሟል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር በነበረው ጨዋታ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ፈርኦኖቹ ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ አይለው ታይተዋል። በተለይም በሰዒድ ሀብታሙ ጥረት የዳኑት የመሐመድ አህመድ እና መሐመድ አብደላ የግንባር ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ሆኖም 38ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ከኦውማር ማርሙሽ የተደረገበትን የርቀት ሙከራ ሲመልስ በአቅራቢያው የነበረው ሙስጠፋ መኪ አስቆጥሮ ግብፅን መሪ አድርጓል።

በንፅፅር ሳቢ የሚባል እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ጥሩ የማጥቃት ሂደቶች ታይተዋል። በተለይም ከሽመልስ በቀለ ተቀይሮ መግባት በኋላ ተነቃቅተው የታዩት ዋልያዎቹ በዳዋ ሆቴሳ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም በአቤል ያለው አማካይነት የተሻሉ ሦስት የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። ሆኖም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በግብፅ ብሔራዊ ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ግንቦት 28 2014 በማላዊ አቻው 2-1 ተሸንፎ የምድብ ማጣሪያውን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ብቻ በማስመዝገብ በቀሩት ጨዋታዎች ተሸንፎ የማጣሪያ ጉዞውን በአራት ነጥቦች ጨርሷል።